1 / 8
ደ/ብርሃን፣ ግንቦት 29/2018 (ሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት)
በተመረጡ የህግ ጉዳዮች ላይ የውይይት መነሻ ሀሳቦች በተለያዩ ዳኞች እየቀረቡ በየ 15 ቀኑ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በስሩ ባሉ ሁሉም ወረዳ ፍርድ ቤቶች የሚካሄደው መደበኛ የዳኞች ሙያዊ የውውይት መድረክ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የዞኑ ዳኞች በሚቀርቡ የውይይት ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ መረዳት እንዲኖራቸው ከሚቀርቡላቸው ጉዳዮች፣ ካስተላለፉት ውሳኔዎች እና በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ካሁን በፊት በሰበር ከተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎች ላይ ምሳሌዎችን እያነሱ ሰፊ ውይይት እያደረጉ እና በጉዳዮቹ ላይ ተቀራራቢ ሀሳብ በመያዝ ላይ ይገኛሉ።
በየ 15 ቀኑ መካሄዱን የቀጠለው የዳኞች መደበኛ የሕግ ውይይት ፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ደረጃ በዛሬው እለት የተካሄደ ሲሆን፣ ትኩረቱ 3ኛ ወገኖች የክርክር አካል ከሚሆኑባቸውና ከዚህ ጋር በተያያዘ በተግባር የሚነሱ አከራካሪና ትኩረት የሚሹ ነጥቦች ላይ አድርጓል፡፡
የውይይት መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የችሎት ሰብሳቢ ዳኛ፣ ክቡር ዳኛ አቶ አያሌው ነብዩ ሲሆኑ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዮሐንስ ወንድሙ ደግሞ ፣ በእለቱ በቀረበው መነሻ ሀሳብ ዳኞችን አወያይተዋል።
በክርክር ሂደት ተሳታፊ መሆን የሚገባቸው ወገኖች ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ማድረግ ለፍርድ ቤትም ሆነ ለተከራካሪዎቹ የራሱ የሆነ ጥቅሞች እንዳሉት የእለቱ አቅራቢ ዳኛ የገለፁ ሲሆን 3ኛ ወገኖች ወደ ክርክር የሚገቡበት በዋናነት በ3 መንገዶች ሊገቡ እንደሚችሉ አንስተዋል፡፡ እነሱም በተከራካሪ ወገኖች ጠያቂነት ፣በራሳቸው አነሳሽነት እና በፍርድ ቤት ትእዛዝ አማካኝነት ሊገቡ እንደሚችሉ ገልፀው በእዚህም ላይ በችሎት የገጠማቸውን ገጠመኞች እንዲሁም ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን አንስተው ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
ሌለው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ስርዓት አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/2016ዓ/ም አንቀፅ 5/4/ ስር በተጠቀሰው ላይ ሊያወያዩ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማዘጋጀት ያቀረቡት የፍርድ ቤት መር አስማሚ ዳኛ አቶ ጣሰው በጋሻው ለተሰብሳቢ ዳኞች አቅርበው ሰፊ ውይይት አድርገዋል ለተነሱትም ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለበለጠ መረጃ
በTelegram:https://t.me/nszhc
በFacebook:https://web.facebook.com/nszhc የሚለውን ማስፈንጠሪያ ተጭነው በመግባት like እና share በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ